ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠትና የህብረተሰቡን አዳጊ ፍላጎት ለማርካት የሰው ሀብት ልማት ወሳኝ መሆኑ ተገለፀ

Unti12

የአዲስ አበባ መለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ በለውጥ ሠራዊት ግንባታና ትግበራ ዙሪያ ከቂርቆስ እና ከአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ለተወጣጡ አመራሮች ለሁለት ቀን ስልጠና ሰጥቷል፡፡ ስልጠናውን የሰጡት የአካዳሚው የአካዳሚክ ጉዳዮች ዳይሩክቶሬት ዳይሬክተር ዶክተር ገብረ ምሩፅ እንደገለፁት የተለዋዋጩ ዓለም እውነታ እንደሚያሳየው በህብረተሰቡ ውስጥ ያለው አዳጊ ፍላጎትና ፋላጎቱን ለማርካት የሚሰጠው ጥራት ያለው አገልግሎት እውነተኛ መስተጋብር የተጣጣመ አይደለም፡፡ በሀገራችንም የሚታየው እውነታ ይኸው ነው፡፡ ስለዚህ ይህን ችግር ለመፍታት ጥራት ያለው አገልግሎት በመስጠት ተገልጋዩን ማርካት የሚችል ብቁ የሰው ሀብት ልማት ማፍራት ለነገ የማይባል ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡ ዳይሬክተሩ በጥናታቸው እንዳብራሩት የመንግስት ሠራተኛው የለውጥ ቡድንን ከፖለቲካ አደረጃጀት ጋር በማያያዝ ችላ ማለት በሌላ በኩል አመራሩ በእውቀት ላይ ተመስርቶ መምራት ባለመቻሉ የሚፈለገውን ለውጥ ማጣት አልተቻለም፡፡ ነገር ግን የለውጥ ቡድን ግንባታውን በአግባቡ መተግበር ከተቻለ ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት፣ ያልተማከለ ህዝባዊ አስተዳደር ለማስፈን፣ የቡድንና የግለሰብ ብቃትን ለመለካትና ለማበረታታት፣ አመራሮችን ለማብቃትና በቴክኖሎጂ ለመደገፍ እንደሚያስችል ጠቁመዋል፡፡

ከሰልጣኞች መካከል አቶ ማስረሻ ተክሉ እና አቶ ሽመልስ ላቀው በሰጡት አስተያየት በስልጠናው የለውጥ ሰራዊት ግንባታ አስፈላጊነትና የሚያበረክተውን አስተዋፅኦ በጉልህ የተገነዘብንበት ነው፡፡ ወደ ስራ ቦታችን ስንመለስም በወሰድነው ስልጠና መሰረት ከሰራተኞቻችን ጋር የጋራ መግባባት በመፍጠር ትኩረት ሠጥተን የምንተገብረው ይሆናል ብለዋል፡፡ አካዳሚው ይህን ስልጠና ማዘጋጀቱ የነበረብንን ክፍተት እንድንሞላ ዕድል ስለፈጠረልን ሊመሰገን እንደሚገባም ጨምረው ተናግረዋል፡፡

የአካዳሚው ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የስልጠናና ማማከር ዘርፍ ኃላፊ የሆኑት አቶ ዮሴፍ አርጋው የስልጠናውን መጠናቀቅ አስመልክተው እንደተናገሩት የለውጥ ስራ ከተጀመረ ዓመታት ቢቆጠሩም የሚፈለገውን ያህል ለውጥ ማምጣት ባለመቻሉ ይህን ስልጠና መስጠት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ እናም ስልጠናውን የወሰዳችሁ አመራሮች በየተቋማችሁ በሰራተኛው መካከል በቂ ግንዛቤ በመፍጠር የተሟላ እምነት ተይዞበት እንዲተገበር ማድረግ ይጠበቅባችኋል ብለዋል፡፡ እንደ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ አደረጃጀት መፍጠር ብቻውን ግብ አይደለም፤ስለሆነም የለውጥ ስራዎችን ውጤት እንደሚያመጡ በማመንና ተግባራዊ በማድረግ የሀገራችን የልማት ጉዞ ማፋጠን እንደሚገባ በአፅንኦት አስገንዝበዋል፡፡

በስልጠናው ከ400 በላይ አመራሮች መሳተፋቸውን መረዳት ተችሏል፡፡      

Posted in Uncategorized.

Leave a Reply

Your email address will not be published.