የአዲስ አባባ መለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ በአመራር ጥበብና በውሳኔ ሰጪነት ዙሪያለወረዳ አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት ሲሰጥ የነበረውን ስልጠና ማጠናቀቁ ተገለጸ

የአዲስ አባባ መለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ በአስሩም ክፍለ ከተሞች ለሚገኙና በወረዳ ደረጃ የወረዳውን ካቢኔ አስተባብረው የሚመሩ የወረዳ አስተባባሪ ኮሚቴዎችን በአራት ዙር በመከፋፈል ከየካቲት 17 እስከ መጋቢት 12/2009 ዓ.ም በተለያየ ጊዜ ለ16 ቀናት ያህል በአመራር ጥበብና ውሳኔ ሰጪነት ዙሪያ ሲሰጥ የቆየው ስልጠና መጠናቀቁን የአካዳሚው የስልጠና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ጉራራ ገለፁ፡፡
አካዳሚው በየወረዳው ለሚገኙ አስተባባሪዎች በአመራርና በውሳኔ ሰጪነት ዙሪያ ያሉባቸውን ክፍተቶች በጥናት ከለየ በኋላ ክፍተቶችን በስልጠና መሙላት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል ያሉት ዳይሬክተሩ ከከተማው አስተዳደር እና ከኢህአዴግ ጽ/ቤት ጋር በጋራ በመነጋገር ለህዝብ ቅርብ ለሆኑ የወረዳ አመራሮች ስልጠና እንዲሰጥ መግባባት ላይ መደረሱንና 585 አመራሮችን ለማሰልጠን ዕቅድ ተይዞ ለ544 አመራሮች ስልጠና በመሰጠቱ የዕቅዱን 93 በመቶ ተግባራዊ ማድረግ እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡
በስልጠናው አመራር ከስራ አመራር ወይም ከአስተዳደር የሚለይበት፣ የአመራር ዘይቤዎችና የአመራር ተግባቦት እንዲሁም የመልካም አስተዳደር መርሆዎችን እንዲያካተቱ ተደርጓል፡፡ በተጨማሪም በውሳኔ ሰጪነት ላይ የሚሳተፉ አካላትን መለየትና አመራሩ ሊከተላቸው የሚገባ የስነ-ምግባር መርሆዎችም የስልጠናው አብይ ርእሶች ሆነው እንዲቀርቡ ተደርጓል፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ አመራሮቸ በወሰዱት ስልጠና መሰረት በሚመሩት ተቋምና በሚያስተባብሩት ወረዳ የሚስተዋሉ የአመራር እና የውሳኔ ሰጪነት እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመቅረፍ የህብረተሰቡን ቅሬታ ይፈታሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በመጨረሻም ስልጠናው በተያዘለት ዕቅድ መሰረት ግቡን የመታ ቢሆንም በተለይ የአራዳ ክፍለ ከተማ በ4ኛው ዙር ምንም ሰልጣኝ አለማሳተፉ እንደ ክፍተት ተወስዷል፡፡ በሌላ በኩል ስልጠናውን ከወሰዱት 544 አመራሮች ውስጥ ሴቶች 46 ብቻ መሆናቸው ከተማ አስተዳደሩ ሴቶችን ወደ አስተባባሪ ደረጃ በማድረስና በማብቃት ረገድ ገና ብዙ ስራ የሚጠብቀው መሆኑን ያመለክታል ሲል ዳይሬክተሩ ጨምረው ገልፀዋል፡፡

Posted in Uncategorized.

Leave a Reply

Your email address will not be published.