የአዲስ አበባ ሴት አመራር ሰልጣኞች በአደጋው ለተጎዱ ወገኖች የ41 ሺ ብር ድጋፍ አደረጉ

የአዲስ አበባ መለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ የሚያሰለጥናቸው የአዲስ አበባ ሴቶች ሊግ አመራር ሰልጣኞችበአዲስ አበባ ከተማ ልዩ ስሙ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በቆሻሻ ክምር መደርመስ ምክንያት ለተጎዱና ቤት ንብረታቸውን ላጡ ወገኖች በቀን ከተመደበላቸው ወጪ ላይ በመቀነስ እና ከግላቸው በማዋጣት የአርባ አንድ ሺ ብር ድጋፍ ማድረጋቸውን የአካዳሚው የፋሲሊቲ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ወይኒቱ ወንድራድ አስታወቁ፡፡
አካዳሚው ከየካቲት 24/ 2009 ዓ.ም ጀምሮ ከአዲስ አበባ ከተማ ከ10ሩም ክፍለ ከተማ ለተወጣጡና ለ15 ተከታታይ ቀናት የሚያሰለጥናቸው ቁጥራቸው ወደ 327 የሚጠጉ ሴት አመራር ሰልጣኞች አደጋው እንደተሰማ በየቀኑ ከሚቀርብላቸው ምግብ ላይ በመቀነስ 26ሺ 982 ብር እንዲሁም በየቡድናቸው በግል 14 ሺ ብር በማዋጣት በድምሩ 40 ሺ 982 ብር ለተጎጂ ወገኖቻቸው እንዲሰጥ ማድረጋቸውን ዳይሬክተሯ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ልዩ ስሙ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ መጋቢት 2/ 2009 ዓ.ም ምሽት ላይ በተፈጠረው የቆሻሻ ክምር መደርመስ ምክንያት ህይወታቸውን ላጡ ወገኖች እንዲሁም ሴቶችና ህጻናት ሰልጣኞቹ መሪር ሃዘን የተሰማቸው መሆኑን በመግለጽ ለቤተሰቦቻቸውና ለወዳጅ ዘመዶቻቸው መጽናናትን ተመኘተዋል፡፡

Posted in Uncategorized.

Leave a Reply

Your email address will not be published.