የአዲስ አበባ መለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ ከ272 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ለሚያስገነባው ጊዜያዊ የአመራር ማሰልጠኛ ማዕከል ግንባታ የውል ስምምነት ተፈራረመ፡፡

አካዳሚው አያት አካባቢ በተረከበው 2.2 ሄክታር መሬት ላይ ጊዜያዊ የአመራር ማሰልጠኛ ማዕከል ለማስገንባት ሚያዝያ 5 ቀን 2009 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ጋር በኔክሰስ ሆቴል የውል ስምምነት ተፈራርሟል፡፡
የውል ስምምነቱን የፈረሙት የአዲስ አበባ መለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር አቶ ካህሰ ወልደማርያም እና የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ወንድሙ ሴታ ሲሆኑ ግንባታውን ከ6 አስከ 8 ወራት ባለው ጊዜ ውስጥ ሰርቶ ለማጠናቀቅ ጥረት እንደሚያደርጉ ዋና ስራ አስፈፃሚው አቶ ወንድሙ ሴታ በዕለቱ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
የአካዳሚው ዋና ዳይሬክተር አቶ ካህሰ ወልደማርያም በበኩላቸው እንደገለፁት ኮርፖሬሽኑ በገባው ቃል መሰረት ግንባታውን በአጭር ጊዜ ውስጥ አጠናቆ እንደሚያስረክብ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም ግንባታው ሲጠናቀቅ ከዚህ በፊት የነበረብንን የስልጠና ቦታ ችግር በመቅረፍ በአዲስ አበባ ከተማ ብቁ አመራር እና የሰው ሀይል ለመገንባት የምናደርገውን ጥረት በማፋጠን ረገድ የጎላ ሚና ይጫወታል ብለዋል፡

Posted in Uncategorized.

Leave a Reply

Your email address will not be published.