የአዲስ አበባ መለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ በአመራር አቅም ግንባታና ልማታዊ ሠራዊት ላይ ያተኮረ የጥናትና ምርምር ሲምፖዚየም ግንቦት 1 ቀን 2009 ዓ.ም በዓዳማ ከተማአካሄደ

tegየአዲስ አበባ መለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር አቶ ከሐሰ ወልደማርያም ሲምፖዚየሙን ሲከፍቱ እንደተናገሩት አካዳሚያችን በ2008 በጀት ዓመትና በ2009 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ያካሄዳቸውን የጥናትና ምርምር ውጤቶችን በሀገር አቀፍ የምርምር ሲምፖዚየም አማካኝነት በየደረጃዉ ለሚገኘ ባለድርሻ አካላት እንዲደርስ እንዲሁም የሲምፖዚዬሙ ተሣታፊ አመራሮች የምርምር ውጤቶችንና የመፍትሔ ሀሳቦችን ከራሳቸው ተቋም ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማገናዘብ እንዲጠቁሙ ለማስቻል ዓላማ ያደረገ መድረክ ነው ብለዋል፡፡ እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ አመራሮች የጥናቱን ግኝት በትኩረት በመመርመር በጥንካሬ የታዩትን አጠናክሮ ማስቀጠል እጥረቶቹን ደግሞ በፍጥነትበማስተካከል የተቀላጠፈ አገልግሎት በመስጠት የከተማችን ሁለንተናዊ ህዳሴ ማረጋገጥ ይገባል ሲሉ በመክፈቻ ንግግራቸው አስረድተዋል፡፡
የለውጥ ሠራዊት ግንባታና ትግበራ በአዲስ አበባ ክፍለ ከተሞች ንፅፀራዊ ትንታኔ ምን እንደሚመስል የአካዳሚው የትምህርትና ስልጠና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ገብረ ምሩፅ ጥናታዊ ፅሁፍ አቅርበዋል፡፡
ዶክተር በጥናታዊ ፅሁፋቸው እንዳብራሩት ከ10 ክፍለ ከተሞች ውስጥ 10 ወረዳዎችን በናሙናነት የተጠቀሙ ሲሆን በሁሉም ወረዳዎች የተለያያ አመለካከትና ተግባር እንዳለ አሣይተዋል፡፡ የለውጥ ሠራዊት ፅንሰ ሀሳብና ትግበራ፣ የሲቪል ሰርቪስ ተቋማት የማመዛዘን ሂደት፣ ለውጥን የመምራት፣ የአመራር ቁርጠኝነት እና መሰል ጉዳዮች በጥናቱ ትኩረት የተደረገባቸው ጉዳዮች ነበሩ፡፡
የለውጥ ሠራዊት ሀገርኛ ትርጉም በግለፅ የተቀመጠ ቢሆንም በለውጥ ሠራዊት አባላቱ በትክክል እንዳልሰረፀ ጥናቱ አመልክቷል፡፡
ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጀማሪ አመራሮች የተሰጠው የአመራር ስልጠና ውጤታማነት ጥናትም በሲምፖዚየሙ ቀርቦ ውይይት ተደርጐበታል፡፡ ጥናቱን ያቀረቡት በአካዳሚው የጥናትና ምርምር ቡድን መሪ የሆኑት አቶ ተገኝ ገበያው ሲሆኑ በ2006 እና 2007ዓ.ም የጀማሪ አመራር ስልጠና የወሰዱ የአዲስ አባ ከተማ አስተዳደር አመራሮች በአራቱ መመዘኛዎች ማለትም በዕውቀት፣ በክህሎት በአመለካከትና ስነ-ምግባር እንዲሁም በተቋማቸው አሰራር ላይ በተጨባጭ ያስገኙትን ውጤት ተንትነው አስረድተዋል፡፡
አቶ ተገኝ በጥናታቸው እንደገለፁት ጀማሪ አመራሮች ስልጠና ከወሰዱ በኋላ በስራ አፈጻጸማቸው ጥናት በተደረገባቸው አብዛኞቹ ወረዳዎች የተሻለ ሆኖ መገኘቱን መረዳት ተችሏል ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢህአዴግ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ተወልደ ገብረፃድቃን በበኩላቸው እንደዚህ አይነት ጥናታዊ ፅሁፎች ያለንበትን ደረጃ እንድናውቅና በፍጥነት ከችግር እንድንወጣ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ እናም ለአካዳሚው ምስጋና ይገባዋል ካሉ በኋላ ጥናቱ ሁሉንም ጉዳይ ያነሣል ተብሎ ባይጠበቅም የቀረበው ጥናት ብዙ ፍንጭ የሚሰጠን በመሆኑ ሁሉም የሲምፖዚየሙ ተሳታፊ አመራሮች ወደ ተቋማችሁ በመውሰድ በፍጥነት መተባበር ይጠበቅባቸዋል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
አንዳንድ የሲምፖዚየሙ ተሳታፊ አመራሮች በሰጡት አስተያየት በቀረበው ጥናት እረክተናል ከተማችን በምን ደረጃ ላይ እንደምትገኝም አሳይቶናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ አስተያየት ሰጪዎቹ ጨምረው እንደገለፁት ጥናቱን መሰረት በማድረግም የተሻለ ስራ ለመስራትና አገልግሎት ለመስጠት ብሎም የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በፍጥነት ለመቅረፍ ተዘጋጅተናል ብለዋል፡፡
በመደረኩ የተለያዩ ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን በሚመለከታቸው አካላት ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ በሲምፖዚየም ላይ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከሁሉም ወረዳዎች የተውጣጡ ከ160 በላይ አመራሮችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

Posted in Uncategorized.

Leave a Reply

Your email address will not be published.