የአዲስ አበባ መለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ የ6 ወር የዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ አካሄደ

Untitled3

አካዳሚው የሁለተኛውን ሩብ ዓመት የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት መጋት 4 ቀን 2010 ዓመተ ምህረት ገምግሟል፡፡ ሪፖርቱን ያቀረቡት የአካዳሚው የዕቅድ ዝግጅት ክትትልና ግምገማ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ደሳለኝ በሪፖርታቸው እንዳብራረሩት አካዳሚው በልማታዊ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ የተቃኘ ትምህርትና ስልጠና፣ ጥናትና ምርምር አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

አካዳሚው ለለውጥ ስራዎች ትኩረት በመስጠት በተለይም የተጠናከረ የልማት ሠራዊት በመፍጠር የተሻለ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥራ እያከናወነ ነው፡፡ ቡድኖችን መልሶ በማደራጀት ዕቅድ አዘጋጅተው ወደ ስራ እንዲገቡ በመደረጉ በዕቅዳቸው መሰረት አደረጃጀቶቹ አጀንዳ እየቀረፁ ከአበይት ተግባራት ባሻገር የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባርን እንዲሁም የመልካም አስተዳር ችግሮችን በተመለከተ አጀንዳ በመቅረፅ እርስ በርሳቸው በመገነባባት ላይ እንደሚገኙ በሪፖርቱ ተብራርቷል፡፡

የሁለቱ ህንፃ ግንባታዎችን በተመለከተ በተለይ አያት የሚገኘው የስልጠና ማዕከል ህንፃ ግንባታ በአንደኛው ሩብ ዓመት በዝቅተኛ አፈፃፀም ላይ እንደሚገኝ መገምገሙን ተከትሎ በተደረገው ከፍተኛ ክትትል በአሁኑ ወቅት በጥሩ አፈፃፀም ላይ ይገኛል፡፡ የዋናው ህንፃ ግንባታ ግን የዲዛይን ችግሮች ያሉበት በመሆኑ የሚፈለገውን ያህል መሄድ ባይችልም የተለያዩ የቅደመ ዝግጅት ስራዎች እየተጠናቀቁ እንደሚገኙ ተገልጧል፡፡ በአጠቃላይ በግምገማው የቁልፍና አበይት ተግባራት አፈፃፀም በስፋት ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን በ6 ወሩ አካዳሚው የተሻለ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡ ከወይይቱ ተሳታፊዎችም የተለያዩ ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን በሚመለከታቸው የስራ ኃላፊዎች ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

በመጨረሻም የአካዳሚው ዋና ዳይሬክተር አቶ ከሀሰ ወልደማርያም ግምገማውን ሲያጠቃልሉ እንደተናገሩት በ6 ወሩ ከሞላ ጎደል ጥሩ እንቅስቃሴ ቢኖርም አሁንም ጉድለቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡ በተለይ የበጀት አፈፃፀሙ ደካማ ነው፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ የህንፃ ግንባታዎች መጓተትና ያለንበት ወቅታዊ ሁኔታ አመቺ አለመሆኑ በምክንያትነት ተጠቅሷል፡፡ ጀኢጅን በተመለከተም ከፌዴራል መለስ አካዳሚ መረጃውን በማምጣት ወደ ስራ የተገባ ሲሆን ያልተጠኑ የስራ መደቦችን በፍጥነት በማጠናቀቅ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ እንደሚደረግ የገለፁት ዋና ዳይሬክተሩ ከትምህርት ዝግጅት አኳያ አካዳሚያችን ሲታይ ከሁሉም የክልል አካዳሚዎች የተሻለ አፈፃፀም እንዳለው አብራርተዋል፡፡ በዚህ ሁለተኛ ሩብ ዓመት በጥንካሬ የታዩትን አጠናክሮ በማስቀጠል በክፍተት የተገመገሙትን ደግሞ ትኩረት ሰጥቶ በመፈፀም የአካዳሚውን ተልዕኮ ለማሳካት ሁሉም የተቋሙ ማህበረሰብ መረባረብ እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

 

 

Posted in Uncategorized.

Leave a Reply

Your email address will not be published.