የአካዳሚው ማህበረሰብ ለሠላም መረጋገጥ ዘብ መቆም እንዳለበት ተጠቆመ

Unti13

የአዲስ አበባ መለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ አመራሮችና ሠራተኞች የካቲት 9 ቀን 2010 ዓመተ ምህረት በሀገራችን ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ውይይት ባካሄዱበት ወቅት የአካዳሚው ምክትል ዋና ዳይሬክተር እና የስልጠናና ማማከር ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዮሴፍ አርጋው የውይይት መነሻ ሀሳብ ሲያቀርቡ እንደተናገሩት ሀገራችን ኢትዮጵያ ከራሷ አልፎ ለጎረቤት ሀገሮች ሠላምን በማስፈን ተግባር ተጠቃሽ ናት፡፡ ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የሚታዩ የፀጥታ ችግሮች ሠላማችንን አደጋ ላይ እየጣለው ይገኛል ብለዋል፡፡

ቀደም ባሉት ጊዜያት በሠላም እጦት የተሠቃየው ህብረተሰባችን የሠላምን ዋጋ ጠንቅቆ ቢረዳም በመልካም አስተዳደር እና በኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮች ሳቢያ ስር የሰደዱ ችግሮች ለሠላማችን መደፍረስ ምክንያት እንደሆኑ አብራርተዋል፡፡

እንደ አቶ ዮሴፍ ገለፃ መንግስት ሠላምና መረጋጋትን ለመፍጠር እስረኞችን ከመፍታት ጀምሮ የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል፡፡ እኛም የአካዳሚው አመራሮችና ሰራተኞች ከመንግስት ጎን በመቆም ለህብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት በመስጠት የተለመደውን የከተማችንን የተረጋጋ ሠላም ማስቀጠል እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

ከተሰብሳቢዎች መካከል አንዳንዶቹ በሰጡት አስተያየት ሠላም የሁሉም ነገር መሠረት ነው፤ስለዚህ ለሠላም መደፍረስ ምክንያት የሚሆኑ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የተሻለ አገልግሎት በመስጠት እና እርካታን በመፍጠር ሠላማችንን ብሎም ልማታችንን ለማረጋገጥ  ቆርጠን ተነስተናል ብለዋል፡፡

በመጨረሻም የአካዳሚው ምክትል ዋና ዳይሬክተር እና የጥናትና ምርምር ዘርፍ ኃላፊ አቶ ጥላሁን ሮባ ውይይቱን ሲያጠቃልሉ እንዳሉት የመንግስት ተቋማት በፍትሀዊነት ህብረተሰቡን ማገልገል ከቻሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ በመቅረፍ ሠላምና ፀጥታን ማስፈን ይቻላል፡፡ ስለዚህ እኛም የህዝብ አገልጋዮች በመሆናችን ተግባራችንን በንቃት በመወጣትና ሠላምን በመጠበቅ የተጀመረውን ልማት ማፋጠን እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ በዘለለ የከተማችንን ፀጥታ አደጋ ላይ የሚጥሉ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ ፈጥኖ ለሚመለከተው አካል ማሳወቅ እንደሚገባም አቶ ጥላሁን አሳስበዋል፡፡     

Posted in Uncategorized.

Leave a Reply

Your email address will not be published.