የሴቶችን ሁለንተናዊ ለውጥ በማረጋገጥ የሀገራችንን የህዳሴ ጉዞ ማፋጠን እንደሚገባ ተገለፀ

Untitled4

የአዲስ አበባ መለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ በዓለም ለ107ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ42ኛ ጊዜ የተከበረውን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን መጋቢት 5 ቀን 2010 ዓመተ ምህረት አክብሯል፡፡ በበዓሉ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአካዳሚው ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የአስተዳደር ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አሰፋ አስፈራው እንዳሉት ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ስናከብር በሀገራችን በልማት፣ በሰላምና በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ዙሪያ ሴቶች ያበረከቱትን ሚና የምናስብበት ነው፡፡ በተለይ ባለፉት ዘመናት በወንዶችና በሴቶች መካከል የነበረውን ልዩነት ለማጥበብ በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ ስራ እየተሰራ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ተጨባጭ ለውጦችን ማየት ጀምረናል ብለዋል፡፡

እንደ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ ሴቶች በትጥቅ ትግሉ በከፈሉት መስዋዕትነት ሀገራችን አሁን ላለችበት ደረጃ እንድትበቃ አድርገዋል፡፡ ከዚህ ባለፈም የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እና ኪራይ ሰብሳቢነትን እንዲሁም የትኛውንም የፀረ ሰላም እንቅስቃሴ የሚጠሉና አምርረው የሚታገሉ ናቸው፡፡ ከምንም በላይ ትውልድ እንዲቀጥል በማድረግ ረገድ ተኪ የላቸውም ያሉት ኃላፊው በተደራጀ የሴቶች ተሳትፎና ንቅናቄ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እናረጋግጣለን የሚለውን መሪ ቃል ተግባር ላይ በማዋል በየትኛውም መስክ ተወዳዳሪና አሸናፊ ማድረግ ኩሁሉም እንደሚጠበቅ በአፅንኦት አስረድተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች ሊግ ኃላፊ ወይዘሮ የሺ ወልዴ በአካዳሚው የስርዓተ ፆታ ክፍል በሴቶች ላይ ትኩረት አድርጎ የተዘጋጀውን ዘጋቢ ፊል መነሻ አድርገው እንደ ተናገሩት ታስቦበት እንደዚህ አይነት ዝግጅት መቅረቡ አካዳሚው ለከተማችን ምሳሌ የሚሆን ነው፡፡ ቀደም ባሉት ጊዜያት ሴት የሚለው ቃል እንደ ስድብ ይቆጠር እንደነበር አይዘነጋም ያሉት ወይዘሮ የሺ አሁን ግን እኩል የልማቱ ተሳታፊዎችና ተጠቃሚዎች መሆን እንደቻሉ አስረድተዋል፡፡ ቢሆንም ግን ዘመኑ ከደረሰበት ስልጣኔ እኩል ለመራመድ ገና ብዙ የሚቀሩ ስራዎች ስላሉ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባል፡፡ የሴቶች ውሳኔ ሰጪነት የሚረጋገጠው የአመራርነት ቦታ ሲሰጣቸው ብቻ ሳይሆን በቤት ውስጥም ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ እናም ሴቶች በከተማችን በየትኛውም ዘርፍ ያላቸው ተሳትፎና ተጠቃሚነት የሚያበረታታ በመሆኑ ይህ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሁሉም ዜጋ ኃለፊነት ሊሆን ይገባል፡፡ ምክንያቱም ሴቶችን ያላሳተፈ ስራ በአንድ እጅ ብቻ እንደመስራት ስለሚቆጠር እኩል በማሳተፍ የሀገራችንን የልማት ጉዞ አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡

ከበዓሉ ተሳታፊዎች መካከል አንዳንዶቹ በሰጡት አስተያየት በአካዳሚያችን የሴቶች ቁጥር ከወንዶች መብለጡ አድለኛ ቢያደርገንም በአግባቡ ግን እየተጠቀምንበት አይደለም፡፡ ሴቶችን በማብቃት ረገድ የሚሰሩ ስራዎች ውስንነት ያለባቸው በመሆናቸው በቀጣይ ትኩረት ሊሠጠው ይገባል ብለዋል፡፡አስተያየት ሰጪዎቹ አክለውም በዓሉን በዓመት አንዴ ብቻ አስቦ መዋል ሳይሆን በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችን ልንተገብረው ይገባል ሲሉ ገልፀዋል፡፡

በዓሉ በተደራጀ የሴቶች ተሳትፎና ንቅናቄ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እናረጋግጣለን በሚል መሪ ቃል በሻማ ማብራት፣ በፓናል ውይትና በሌሎች ዝግጅቶች በድምቀት ተከብሮ ውሏል፡፡         

Posted in Uncategorized.

Leave a Reply

Your email address will not be published.