የህጻናት ማቆያ ማዕከልን ለማቋቋም የሚያግዙ ተግባራት እየተከናወኑ ነው፡፡

የአዲስ አበባ መለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ ከ200 ሺ ብር በላይ በጀት በመመደብ የህጻናት ማቆያ ለማደራጀት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የአካዳሚው ስርዓተ ጾታ ክፍል ኃለፊ ወ/ሪት አዜብ ገበያ ገለጹ፡፡
ኃላፊዋ እንደተናገሩት ቀደም ሲል የአካዳሚው ሴት የመንግስት ሰራተኞች የህጻናት ማቆያ ባለመኖሩ ሳቢያ ልጆቻቸውን ይዘው ወደ ስራ ቦታ የመምጣትና አልፎ አልፎም ስራቸውን የመልቀቅ ዝንባሌ እንደነበራቸው ጠቅሰው ችግሩ ከእናቶች ባለፈ ቤተሰብ ላይ ከፍተኛ ስነልቦናዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና እንደነበረው ገልጻዋል ፡፡ በተጨማሪም ለስልጠና የሚመጡ ህጻናት ያላቸው ሴት ሰልጣኞች ከስልጠናው የሚገለሉበት ሁኔታ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
አክለውም አካዳሚው የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ ከሌሎች ተቋማቶች ልምድ እንዲቀሰም በማድረግ በያዝነው በጀት ዓመት በተቋሙ የህጻናት ማቆያ ለማቋቋም ከ200 ሺ ብር በላይ በጀት በመመደብ እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡daycare2
daycare1 የህጻናት ማቆያው በሶስት ምእራፍ ተከፍሎ የሚደራጅ ሲሆን አሁን ካለው የቦታ፣ የሰው ኃይልና የበጀት ችግር አንጻር የመጀመሪያው ምዕራፍ ስራ በቤታቸው የህጻናት ተንከባካቢ የሌላቸው ሴት የመንግስት ሰራተኞችን ችግር ለማቃለል አካዳሚው ካሉት የመኝታ ክፍሎች ውስጥ ሶስቱ እንዲለቀቁ በማድረግ ስራው የተጀመረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት ለህጻናት ማቆያው የሚያገለግሉ አልጋዎች ፣ የህጻናት ወንበርና ጠረጴዛዎች፣ ፍራሽ፣ ፍሪጅ ፣ሼልፍና ልዩ ልዩ የመጫዎቻ ቁሳቁሶች ግዢ መፈጸማቸውን ኃላፊዋ አክለው ገልጸዋል፡፡daycare3
የአካዳሚው የአመራር ስልጠና ቡድን መሪ የሆኑት ወ/ሮ ምህረት ኃ/ መስቀል አካዳሚያችን የስልጠና ተቋም እንደመሆኑ ከዚህ በፊት ለስልጠና ወደ አካዳሚው የሚመጡ ህጻን ልጅ ያላቸው ሴት ሰልጣኞች ልጆቻቸውን የሚንከባከብላቸው ባለማግኘታቸው ስልጠናውን አቋርጠው ይሄዱ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ አክለውም በአሁኑ ሰዓት የህጻናት ማቆያ በአካዳሚው ውስጥ መደራጀቱ የአካዳሚው ሴት ሰራተኞችና ሰልጣኞች ከስጋት ነጻ በመሆን በተሰማሩበት መስክ ውጤታማ ስራ መስራት እነደሚያስችላቸው ገልጸዋል፡፡ አካዳሚው የጉዳዩን አስፈላጊነት በመገንዘብ በቀጣይ የህጻናት ማቆያው ስታንዳርዱን በጠበቀ መልኩ አገልግሎት እንዲሰጥ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

Posted in Uncategorized.

Leave a Reply

Your email address will not be published.