ወጣቱ ራሱን ከኤች አይቪ ኤድስ መጠበቅ እንዳለበት ተገለፀ

hiv1የአዲስ አበባ መለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ ዓለም አቀፍ የኤች አይቪ ኤድስና የነጭ ሪቫንን ቀንን በተለያዩ ዝግጅቶች አስበው ውለዋል፡፡ ቀኑን በማስመልከት የአካዳሚው ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የአአስተዳደር ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ምስራቅ ወርቁ ፕሮግራሙን ሲከፍቱ እንደተናገሩት 65 በመቶ የሚሆነው የህብረተሰብ ክፍል ወጣት በሆነባት ሀገራችን በኤች አይቪ ኤድስ መስፋፋት ምክንያት አምራች የሆነውን ሀይል እያጣን ነው፡፡ እናም ወጣቱ አምራች ብቻ ሳይሆን የነገ ሀገር ተረካቢም ጭምር በመሆኑ ራሱን ከበሽታው ሊጠብቅ እንደሚገባ አስርደተዋል፡፡
የመወያያ ፅሁፍ ያቀረቡት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኤች አይቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት ባለሙያ የሆኑት ሲስተር ሽብሬ መንገሻ በሰነዱ እንዳብራሩት ኤች አይቪ ኤድስ መከሰቱ ከታወቀበት እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ1981 ጀምሮ በዓለም ላይ ከ39 ሚሊዮን የሚልቁ ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል፡፡ በሀገራችንም በርካታ ወገኖቻችንን እንድናጣ ከማድረጉም በላይ ቁጥራቸው አያሌ የሆኑ ህፃናትን ካለወላጅ እንዲሁም አረጋዊያንን ያለጧሪ እንዲቀሩ ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡እንደ ሲስተር የሽብሬ ገለፃ ባለፉት ዓመታት የበሽታውን አስከፊነት በመገንዘብ በሀገራችን ሰፊ የመከላከል ስራ በመሰራቱ በከፍተኛ ደረጃ ስርጭቱን መቀነስ የተቻለ ቢሆንም ከዚህ ጋር ተያይዞ በተፈጠረው መዘናጋት በአሁኑ ወቅት አገርሽቶ አስጊ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ hiv2
በተለይ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተደረገው ጥናት ስርጭቱ በከፍተኛ ደረጃ እየተስፋፋ መሆኑን ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ መንግስትም እንደ በፊቱ ሁሉ ለበሽታው ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኝ ባለሙያዋ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በበሽታው ላይ በመዝመት በአጭር ጊዜ ውስጥ ስርጭቱን መግታት ይገባል ብለዋል፡፡ በተያያዘ ዜና የነጭ ሪቫን ቀንን በማስመልከት የአካዳሚው የስርዓተ ፆታ ክፍል ኃላፊ የሆኑት ወይዘሮ አዜብ ገበያ በፆታዊ ጥቃት ላይ ያጠነጠነ ጥናታዊ ፅሁፍ አቅርበዋል፡፡ ይህ በአካዳሚው ላይ የተደረገው ጥናት እንደሚያስረዳው ግልፅ የሆነ ፆታዊ ጥቃት ባይፈፀምም ሴቶችን ወደ አመራር አለማምጣት፣ ከወንዶች አሳንሶ የማየት፣ የማሸማቀቅ እንዲሁም በቂ የሆነ የትምህርት ዕድል አለመስጠት የሚሉና ሌሎች ተጨማሪ ጉዳዮች ተዳስሰዋል፡፡ በመጨረሻም ከተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን በሚመለከታቸው አካላት ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ የነጭ ሪቫን ቀን በዓለም ለ27ኛ በሀገራችን ደግሞ ለ13ኛ ጊዜ ጀግኒት ልጆቿን በማስተማር ፆታዊ ጥቃትን ትከላከላለች በሚል መሪ ቃል እንዲሁም የኤች አይቪ ኤድስ ቀን በሀገራችን ለ30ኛ ጊዜ ለኤች አይቪ ይበልጥ ተጋላጭ ነን እንመርመር ራሳችንን እንወቅ በሚል መሪ ቃል ታስቦ ውሏል፡፡

Posted in Uncategorized.

Leave a Reply

Your email address will not be published.