ኢትየጵያን ከመበታተን የታደጋትን የፌደራል ሥርዓት ሁሉም ሊጠብቀው እንዳሚገባ ተገለፀ

d2 d1የኢትዮጵያ የፌደራል ስርዓት ባህሪያት፣ ዴሞከራሲያዊ አንድነት ግንባታ ሂደት ስኬቶችና የወደፊት አቅጣጫዎችን አስመልከቶ ለአዲስ አበባ መለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ አመራርና ሠራተኞች ከህዳር 22 እስከ 23/2010 ዓ.ም በጌትፋም ሆቴል ስልጠና ተሰጥቷል፡፡ ስልጠናውን የሰጡት የአካዳሚው የግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬከተር አቶ ደርቤ ፈለቀ በስልጠና ሰነዱ እንዳብራሩት የኢትዮጵያ የፌደራል ስርዓት በዓለም ጨቅላ ዕድሜ ካላቸው አዳጊ የፌደራል ስርዓቶች ውስጥ የሚመደብ እንዲሁም ከአስከፊ የድህነትና የዴሞክራሲ እጦት ደረጀ ላይ ቢጀመርም በአሁኑ ሰዓት ግን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ስኬቶችን በማስመዝገብ ለሌሎች ሀገራትም የሚተርፍ ልምዶችን እያበረከተ የሚገኝ ስርዓት መሆኑ ጠቁማል፡፡
የኢትዮጵያ የፌደራል ሥርዓት ሁሉም የዓለም ፌደራል ሀገራት የሚከተሏቸውን የጋራ ባህሪያት ያሟላ፣ ከራሱ ታሪካዊና ነባራዊ ሁኔታዎች የመነጩ ልዩ ባህሪያት ያሉት ብሎም በሁሉም የዴሞክራሲያዊ ይዘት መስፈርቶች ሲመዘን የላቀ ዴሞክራሲያዊ ይዘት ያለውን ህገ መንግስት በማፅደቅ እየተመራ የሚገኝ ሥርዓት እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ፌደራሊዝም በአለም አቀፍ ደረጃ ለህብረ ብሄር ሀገራት ሁሉ ተመራጭ የአስተዳደር ዘይቤ ሊሆን እንደሚችል ምሁራን ሳይንሳዊ ትንታኔ እየሰጡበት እንደሚገኙ በተለይም ደግሞ ኢትዮጵያን ከመበታተን አደጋ የታደገ ሥርዓት እንደሆነ ዳይሬክተሩ በአፅንኦት አስረድተዋል፡፡
ከተሳታፊዎች መካከል እንዳንዶቹ በሰጡት አስተያየት ስልጠናው የፌደራል ስርዓታችንን በሚገባ እንድንገነዘብ ያደረገ ነው፡፡ እኛም በቀጣይ ስርዓቱን የበለጠ ለማጎልበት ጠንክረን እንሰራለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የአካዳሚው ዋና ዳይሬከተር አቶ ከሀሰ ወልደማሪያም በማጠቃለያ ንግግራቸው እንደገለፁት ያለፉት ሥርዓቶች ህገ መንግስታት የገዥዎችን ፍፁማዊነት በማሣየት ፍላጐታቸውን ለማሣካት የተደነገጉ ነበሩ፡፡ የፌደራል ሥርዓቱ ከተዘረጋ በኋላ ግን ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ ማንነቱ ተከብሮ በመቻቻልና በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ ግንኙነትን ማጠናከር አስችሎታል ብለዋል፡፡ ስለሆነም ፐብሊክ ሠርቪሱ የህዝብ አገልጋይ እንደመሆኑ መጠን በኢትዮጵያ ፌደራል ሥርዓት የህብረ ብሔራዊነት ምንነትን በመገንዘብ የፌደራል ሥርዓት ግንባታ ሂደቱን ማሣካትና ተግዳሮቶቹን በመታገል የኢትዮጵያን ህዳሴ ጉዞ እውን ማድረግ ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

Posted in Uncategorized.

Leave a Reply

Your email address will not be published.