አካዳሚው የአገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን በ1.5 ቢሊዮን ብር ህንጻ እያስገነባ መሆኑ ተገለጸ

የአዲሰ አበባ መለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ የሚሰጠውን አገልግሎት ለማዘመን በቦሌ ክፍለ ከተማ አምቼ አካባቢ በተሰጠው 21740 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ በ1.5 ቢሊዮን ብር ዘመናዊ ህንጻ እያስገነባ መሆኑን የአካዳሚው ዋና ዳይሬክተር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ እስክንድር መኩሪያ ገለጹ፡፡

አካዳሚው በደንብ ቁጥር 67/2007 የተሰጠውን ስልጣንና ተግባር በብቃት በማከናወን አገራችን  የጀመረችውን የህዳሴ ጉዞ ማስቀጠል የሚችል በልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ፍልስፍና የታነጸና ለፖሊስና ስትራቴጂዎች ተግባራዊነት ህብረተሰቡን የማስተባበርና የማሳተፍ ብቃት ያለው አመራር ለመገንባት ደረጃውን የጠበቀና በግብዓት የተሟላ ህንጻ መገንባት አስፈላጊ መሆኑ በቦርዱ ታምኖበት ወደስራ እንደተገባ ኃላፊው አያይዘው ገልጸዋል፡፡

ህንጻው ሲጠናቀቅ  ይህን ይመስላል ፡፡

የህንጻው የዲዛይን ስራ በበረከት ተስፋዩ አማካሪ ድርጅት እንደተሰራ፤ አለም አቀፍ ጨረታው በፌደራል የግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት አማካኝነት እንደወጣና  በርካታ ተጫራቾች እንዲሳተፉበት እንደተደረገ እንዲሁም የሚመለከታቸው የስራ ክፍሎችና ባለሙያዎች በተገኙበት  መስፈርቱን አሞልቶ የተገኘው ዮቴክ ኮንስክትራክሽን ድርጅት ውል እንዲገባ፣ ሳይት እንዲረከብና   ቅድመ ክፍያ እንዲከፈለው በማድረግ  ወደ ግንባታ መግባቱን ኃላፊው ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በአጠቃላይ ህንጻው ሲጠናቅ G+14 ርዝመት እንዳለውና የአስተዳዳር ቢሮ፤ የማሰልጠኛ ክፍሎች፤ የኮምፒዩተር ላብራቶሪ፣ ላይብረሪ፣ የሰልጣኞች ምኝታ ክፍል፤ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ፤ መመገቢያ ክፍሎችና የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች የዘመናዊው ህንፃ ግንባታ አካል መሆናቸውን ጠቁሟል፡፡

የግንባታው ሁኔታ  በአማካሪ ድርጅት እየተደገፈ በጥራትና በውሉ መሰረት  እንዲፈጸም  ከመደረጉ በተጨማሪ  የህንጻ ግንባታውን የሚከታተል አምስት አባላት ያሉት   ኮሚቴ ተቋቁሞ በየጊዜው  ክትትል በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ኃላፊው ተናግረዋል ፡፡

 

Posted in Uncategorized.

Leave a Reply

Your email address will not be published.