አመራሩ ከብረተሰቡ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በፍጥነት በመፍታት የህብረተሰቡን እርካታ ሊያረጋጥ ይገባል ተባለ

የአዲስ አበባ መለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ ለሁለተኛ ዙር መካከለኛ አመራሮች ባዘጋጀው ስልጠና ላይ የአካዳሚው ዋና ዳይሬክተር አቶ ካኸሰ ወልደማርያም በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለፁት አመራሩ ሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በስኬት ለማጠናቀቅ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ ይገባል ብለዋል፡፡ ከምንም በላይ በጥልቅ ተሀድሶው የተለዩና ህብረተሰቡ ያነሳቸውን ችግሮች በአፋጣኝ በመፍታትና የህብረተሰቡን እርካታ በማረጋገጥ ለሀገራችን ህዳሴ መሳካት ሀላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው ዋና ዳይሬክተሩ ጨምረው ገልፀዋል፡፡
እንደ አቶ ከሐሰ ማብራሪያ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተነደፈውን የ2ኛ ዙር የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በውጤታማነት ለመፈፀም አመራሩን በዕውቀት፣ በክህሎትና በአመለካከት ዝግጁ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ በመሆኑም አመራሩ ከአንድ ወር በላይ በሚቆየው በዚህ ስልጠና ላይ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ አቅሙን ማጎልበትና ስራውን በእውቀት መምራት እንዳለበት በአፅንኦት ተናግረዋል፡፡
ከመካከለኛ አመራር ሰልጣኞች መካከል አንዳንዶቹ በሰጡት አስተያዬት እንደገለፁት አካዳሚው ከጥልቅ ተሀድሶ መልስ እንደዚህ ዓይነት ስልጠና ማዘጋጀቱ በተሀድሶው ወቅት የተለዩ ችግሮችን እና መግባባቶች ወደ ተጨባጭ ስራ ለመግባትና ቅሬታዎችን በእውቀት ላይ ተመስርተን ለመፍታት ዕድል ይፈጥርልናል ብለዋል፡፡ አስተያዬት ሰጪዎቹ

አክለውም ስልጠናው ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ በንቃት በመሳተፍ አቅማችንን አጎልብተን ለመውጣት ተዘጋጅተናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ስልጠናው በከፍተኛ አመራሮች የሚሰጥ ሲሆን የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ምንነት፣ታሪካዊ አነሳስ፣ ዕድገትና የወደፊት አቅጣጫ፣ የኢትዮጵያ የፌዴራል ስርዓት፣ የልማታዊና
ዴሞክራሲያዊ አመራር ሳይንስና ጥበብ ለኢትዮጵያ ህዳሴ፣ ልማታዊ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ለኢትዮጵያ ህዳሴ እንዲሁም የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን የተመለከቱና ሌሎች ተጨማሪ ርዕሰ ጉዳዮችን አጀንዳ ያደረገ ነው፡፡
በስልጠናው ላይ ከአራቱም ብሄራዊ ድርጅቶች እና ከሁለቱም ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ 541 ሰልጣኞች የሚሳተፉ ሲሆን ከሐምሌ 19/2009 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ 44 ቀናት እንደሚቆይ መረዳት ተችሏል፡፡
የአዲስ አበባ መለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከ6 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ጀማሪና ተተኪ አመራሮች በሀገራዊ ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ዙሪያ ስልጠ ሰጥቷል፡፡

Posted in Uncategorized.

Leave a Reply

Your email address will not be published.