ታላቁ የህዳሴ ግድብ ከአድዋ ድል ቀጥሎ ህዝቡን በአንድ ልብ ከጫፍ ጫፍ ያንቀሳቀሰ መሆኑ ተገለፀ!

Untitled

የአዲስ አበባ መለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ አመራሮችና ሰራተኞች የታላቁን የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ሰባተኛ ዓመት የምስረታ በዓል ታላቁ የህዳሴ ግድባችን የሀገራችን ህብረ ዜማ፤ የህዳሴያችን ማማ በሚል መሪ ቃል መጋቢት 21 ቀን 2010 ዓመተ ምህረት አክብረው ውለዋል፡፡ በዓሉን በማስመልከት የአካዳሚው የገግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደርቤ ፈለቀ ባቀረቡት የመወያያ ፅሁፍ እንዳብራሩት ሰማያዊ ወርቃችን ይቻላል ብለን መገንባት እንደጀመርነው አጋምሰነዋል፤ እንዳጋመስነው እያገባደድነው፣ እንዳገባደድነው ሁሉ እንጨርሰዋልን የሚለውን አፅንኦት ሰጥተው አስረድተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ከአንድ ምዕተ ዓመት በፊት የቀደሙ እናትና አባቶቻችን በሀገር ውስጥ የትኛውም አይነት የእርስ በርስ ሽኩቻ ሳይበግራቸው ቅድሚያ ለሀገር በመስጠት የሚቻል የማይመስለውን የውጭ ወራሪ አሳፍሮ በመመለስ ድል መንሳት ችለዋል፡፡ የዚህ ዘመን ትውልድም አንዳንድ ልዩነቶች ቢነሩም ልዩነቱን ወደጎን በመተው ቀደምት መንግስታት ከሀሳብ በዘለለ ያልደፈሩትን የአባይን ወንዝ ለመገደብ በአንድነት የተመመበትና ግድቡ አሁን ለደረሰበት ደረጃ እንዲበቃ ያደረገበት ተግባር የሚያኮራ ነው፡፡ የአባይን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ መቀየር በመቻላችን አይችሉም ብለው የሚያስቡ የዓለም ሀገራት ፊታቸውን እንዲያዞሩ የተገደዱበት ጊዜ ላይም እንደምንገኝ ጠቁመዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ ግድቡ የህዳሴያችን ብርሀን ተስፋ የፈነጠቀበት ብሎም ወደ ቀደመ ገናናነታችን የመለሰን በመሆኑ ፍፃሜውን እስከምናይ እና ሀገራችን ያለመችውን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ጎራ የመሰለፍ ራዕይ እስኪሳካ የተጀመረው ርብርብ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ባቀረቡት የመወያያ ሰነድ አስረግጠው ተናግረዋል፡፡

ከተሳታፊዎቹ መካከል አንዳንዶቹ በሰጡት አስተያየት ውይይቱ የበለጠ መነቃቃትና ቁጭት ፈጥሮብናል፡፡ በመሆኑም በተቋማችን የሚታየውን መፋዘዝ በማስወገድ የሚችሉትን ሁሉ ለማድረግ እንደሚጥሩ ተናግረዋል፡፡ የታላቅነታችን ሚስጥር ቁልፍ ያለው በእኛው ትውልድ እጅ  በመሆኑ ታሪክ ለመስራት ተዘጋጅተናል ብለዋል፡፡

በመጨረሻም የአካዳሚው ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የስልጠናና ማማከር ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዮሴፍ አርጋው ውይይቱን ሲያጠቃልሉ እንዳሉት ከእኛ ውጭ ለገራችን ማንም ተቆርቋሪ ሊሆን አይችልም፡፡ ስለዚህ በልዩ የመነቃቃትና የመነሳሳት መንፈስ የተጀመረውን ግድብ ዳር ማድረስ ይጠበቅብናል፡፡ ይህን ስናደርግ አሁን የምናነሳቸው ችግሮች ተቀርፈው የምንፈልገውን ጉዳይ ማሳካት ስለሚቻል ድጋፋችን ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

የአካዳሚው ሰራተኞች በፊት ቃል ከገቡት ገንዘብ በተጨማሪ የቦንድ ሳምንትን ምክንያት በማድረግ በዕለቱ ከ10 ሺህ ብር በላይ ቦንድ መግዛታቸውንም ለማወቅ ተችሏል፡፡ በዓሉ በፎቶ ግራፍ አውደ ርዕይ፣ በሻማ ማብራትና በጥያቄና መለስ ውድድሮች ተከብሯል፡፡                 

Posted in Uncategorized.

Leave a Reply

Your email address will not be published.