በሴቶች ላይ የሚደርሱ አካላዊና ስነ ልቦናዊ ጥቃቶችን ለመከላከል ሁሉም የአካዳሚው ማህበረሰብ የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ ተገለፀ

azየአዲስ አበባ መለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ አመራርና ሰራተኞች ህዳር 26 ቀን 2010 ዓመተ ምህረት የፀረ-ፆታዊ ጥቃት የነጭ ሪቫንን ቀን ባከበሩበት ወቅት የካዳሚው ምክትል ዋና ዳይሬክተር እና የአካዳሚክ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዮሴፍ አርጋው በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለፁት በሴቶች ላይ የሚደርሱ አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጥቃቶችን ለመከላከል ሁሉም የአካዳሚው ማህበረሰብ በተለይም ወንዶች የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ በቀጣይ አካዳሚው አሁን ካለበት በተሻለ መልኩ በሴቶች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡
የአካዳሚው የስርዓተ ፆታ ክፍል ኃላፊ ወይዘሪት አዜብ ገበያ ባቀረቡት የስርዓተ ፆታ ኦዲት ሪፖርት እንዳብራሩት ለሀገራችን ድህነት መንስኤ ሆኖ የቆየው አንዱ ሴቶችን በእኩልነት ከወንዶች ጋር በልማት ማሳተፍ ባለመቻሉ ነው፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ለሴቶች የሚሰጠው ትኩረት እየተሻሻለ መምጣቱ ባይካድም አሁንም አካላዊና ስነ ልቦናዊ ጥቃቶች ሙሉ በሙሉ አልተቀረፉም፡፡ ስለዚህ ሴት ማለት እናት፣እህት፣ሚስት ሁሉንም ነገር መሆኗን በመገንዘብ በተለይ ወንዶች ዘብ ሊቆሙ እንደሚገባ ኃላፊዋ አስረድተዋል፡፡
እንደ ወይዘሪት አዜብ ገለፃ በአካዳሚው የስርዓተ ፆታ ቢሮ መከፈቱ፣ካሉት ሰራተኞች አብላጫውን ቁጥር ሴቶች የሚወስዱ መሆኑ በጥናካሬ የሚታይ ቢሆንም በአመራር ደረጃ የተቀመጡት ግን ቁጥራቸው በጣም ዝቅተኛ ወይም 20 በመቶ ብቻ መሆናቸውን ባቀረቡት ጥናት አመለካክተዋል፡፡ ከዚህ በጨማሪ ከትምህርት ደረጃ እና ከስራ ልምድ አኳያም ከወንዶች በጣም ያነሱ መሆናቸውን የጥናቱ ግኝት አሳይቷል፡፡ ስለሆነም አካዳሚው ሴቶችን በማብቃት የአመራር ሰጪነት ሚናቸውን ማሳደግና በየትኛውም የስራ መስክ በማሰማራት ውጤታማ እንዲሆኑ ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ከተሳታፊዎች መካከል አንዳንዶቹ በሰጡት አስተያየት የሴቶች መብት እየተከበረ ያለ ቢሆንም ጥቃቶች በሚደርሱበት ጊዜ ህብረተሰቡ ጥቆማ መስጠት እንደሚገባው ጠቁመዋል፡፡
በዓሉ በዓለም አቀፍ ለ27ኛ፣በሀገራችን ለ12ኛ እንዲሁም በአካዳሚያችን ለ2ኛ ጊዜ ‹‹በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከልና ለማስወገድ የወንዶች አጋርነትን ማጠናከር›› በሚል መሪ ቃል ዘጋቢ ፊልም በማዘጋጀትና በሻማ ማብራት ስነ ስርዓት ተከብሯል፡፡

Posted in Uncategorized.

Leave a Reply

Your email address will not be published.