ሠላሣ ሁለተኛው የፀረ ኤድስ ቀን ታስቦ ዋለ

ww
ww1
ww4
ww3
የአዲስ አበባ መለስ ዜናዊ ስራ አመራር ኢንሰቲትዩት አመራርና ሰራተኞች በየዓመቱ ህዳር 22 ቀን ተከብሮ የሚውለውን 32ኛውን የፀረ ኤድስ ቀን በተለያዩ ዝግጅቶች አስበው ውለዋል፡፡በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሀፕኮ ጽህፈት ቤት የሜኒስትርሚንግ አጋርና ጥምረት ቡድን መሪ የሆኑት አቶ ወንድሙ ደንቡ ቀኑን በማስመልከት የመያያ ፅሁፍ አቅርበዋል፡፡ በሀገራችን ቀደም ባሉት ጊዜያት በተሰራው ጠንካራ ስራ በኤች አይቪ ኤድስ የሚያዘውንና የሚሞተውን የሰው ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ ተችሎ ነበር፡፡ አሁን ግን የተፈጠረውን መዘናጋት ተከትሎ የቫየረሱ ስርጭት በፍጥነት አድማሱን እያሰፋ መምጣቱን በፅሁፋቸው አመላክተዋል፡፡ የስርጭት ምጣኔውን ለአብነት ብንመለከት በአገራችን 0.9 በመቶ በመዲናችን አዲስ አበባ ደግሞ 3.4 በመቶ እንደደረሰ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ ያለው ስርጭት ወደ ወረርሽኝ ደረጃ መሸጋገሩን አቶ ወንድሙ አብራርተዋል፡፡

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀርጋሞ ሀማሞ በበኩላቸው የአገራችን ዕድገት እውን የሚሆነው አምራችና ጤናማ ዜጋ ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን በዚህ በሽታ ምክንያት ይህን አምራች የሆነውን የህብረተሰብ ክፍል እያጣን እንገኛለን ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ በየትኛውም አጋጣሚ ስለበሽታው ግንዛቤ በመፍጠር ስርጭቱን መከላከልና ህይወትን መታደግ ለአፍታም ቢሆን መዘንጋት እንደሌለበት አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም የኢንስቲትዩቱ ሰራተኞች በበሽታው ወላጆቻቸውን ላጡ 5 ችግረኛ ልጆች ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል፡፡
የዘንድሮው የፀረ ኤድስ ቀን ‹‹ማህበረሰብ የለውጥ አቅም ነው›› በሚል መሪ ቃል ታስቦ ውሏል፡፡

Posted in Uncategorized.

Leave a Reply

Your email address will not be published.