ለኢህአዴግ ሴቶች ሊግ አመራሮች በአዳማ ከተማ ስልጠና መሰጠቱ ተገለጸ

የአዲስ አበባ መለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢህአዴግ ጽ/ቤት እና ከከተማው ሴት ሊግ ጋር በመተባበር ከአስሩም ክፍለ ከተማለተወጣጡ የኢህአዴግ ሴቶች ሊግ አመራሮች በልዩ ልዩ ርዕሰ ጉዳዮች በአሮሚያ አመራር አካዳሚአዳማ ከተማ ላይ ከየካቲት 26/2009 ዓ.ም ጀምሮ ለ15 ተከታታይ ቀናት ስልጠና መሰጠቱን የስልጠናው አደረጃጀት ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ጀንበሩ ኢርኮ አስታወቁ፡፡
አስተባባሪው አክለውም በከተማው ከሚገኙ ከ10ሩም ክፍለ ከተሞችና ከሁሉም ወረዳዎች የተወጣጡ ቀጥራቸው 330 የሚሆኑ የሴት ሊግ አመራሮች ለ15 ተከታታይ ቀናት በሴቶች ሊግ ተልእኮና አደረጃጀት፤ በኢትዮጵያ ፌደራል ስርዓት ባህሪያት፣ የዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባታ ሂደት ስኬቶችና የወደፊት አቅጣጫዎች እንዲሁም በአመራር ጥያቄ ርእሰ ጉዳዮች ላይ የተሰጠውን ስልጠና በተገቢው መንገድ ተከታትለው ማጠናቀቃቸውን ገልጸዋል፡፡
የሴት ሊግ አመራሮቹ በከተማው ውሰጥ የሚገኙ የሊግ አደረጃጀቶችን በማጠናከር የልማታዊ አስተሳሰብ ልእልና እንዲረጋገጥ፣ የሴቶች ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲከዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንዲያድግና ፖለቲካዊ ተሳትፏቸው እንዲጎለብት እንዴት መስራት እንዳለባቸው ስልጠናው ተጨማሪ አቅም እንደ ፈጠረላቸው አስተባባሪው አክለው ተናግረዋል፡፡
ሰልጣኞቹ በቆይታቸው በንድፈ ሀሳብ ደረጃ ያገኙትን ግንዛቤ ይበልጥ ለማስፋትና ሀገራችን በምትገነባቸው ኢንዱስትሪዎች የሚፈጠሩ የስራ ዕድሎች እንዲሁም የቴክኖሎጂ ሽግግር ምን ያህል ሴቶችንና ወጣቶችን ተጠቃሚ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ማሳያ የሆነውን የቢሾፍቱን አውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪን እንዲጎበኙ ተደርጓል፡፡

Posted in Uncategorized.

Leave a Reply

Your email address will not be published.