ለቀጣዩ ትውልድ ኢትዮጵያን አልምተን እና አበጅተን ማሻገር አለብን ተባለ ፡፡

ቀን ሰኔ 03/2013 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ስራ አመራር ኢንስቲትዩት አመራሮችና ሰራተኞች በ2013 ክረምት ኢትዮጵያን እናልብስ በሚል የተዘጋጀው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተካላ ስራን በደመቀ ሁኔታ ለማስጀመር ጎሮ አካባቢ ኢንስቲትዩቱ በሚያስገነባው ህንጻ ቅጥር ግቢ ውስጥ በመገኘት የተተከሉ ችግኞችን የመንከባከብና አዲስ ችግኞችን የመትከል ስራ አከናውነዋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ ኢትዮጵያን እናልብስ በሚል ባዘጋጀው የንቅናቄ ፕሮግራም ላይ የተገኙት የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሐርጋሞ ሐማሞ አባቶቻችን ኢትዮጵያን ሰርተውና አበጅተው ለዛሬው ትውልድ እንዳስረከቡ ሁሉ እኛም የአገራችንን ገጽታ አረንጓዴ አልብሰን እና የተፈጥሮ ሚዛኗን ጠብቀን ለልጆቻችን ማሻገር አለብን ብለዋል፡፡
አካባቢያችንን አረንጓዴ ለማልበስ የምናከናውነው ተግባር በዓመት የሚመጣ መርሃ ግብር ሳይሆን የኃላፊነትና የሞራል ግዴታ ነው፡፡ ስለዚህ ተፈጥሮ የመኖራችን ዋስትና እንደሆነ ተረድተን ችግኞችን በአግባቡ በመትከል፣ በመንከባከብ እና በማሳደግ ለቀጣዩ ተውልድ ማስረከብ ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
በንቅናቄ ፕሮግራሙ ላይ በ2012 ክረምት የተተከሉ ችግኞችን የማረም፣ የመኮትኮትና ውኃ የማጠጣት ስራ የተከናወነ ሲሆን በዕለቱ አዲስ ችግኞችን የመትከል ስራ ተሰርቷል፡፡

Posted in Uncategorized.